Friday, November 9, 2012

አቃቤ መንበር ብፁዕ አቡነ ናትናኤል የቋሚ ሲኖዶስን አልመራም ብለው ከስበሰባ መውጣታቸው ተነገረ


ምንጭ:- http://www.abaselama.org/
Thursday, November 8, 2012

ሮብ እለት 28/2/2005 በጠዋቱ ክፍለ ጊዜ በተደረገው የቋሚ ሲኖዶስ ስብሰባ ላይ ብፁዕ አቡነ ናትናኤል ስብሰባውን በጸሎት እንዲያስጀምሩ ለቀረበላቸው ጥያቄ «የእኔን አቃቤ መንበርነት መች ተቀበላችሁና ነው በጸሎት የማስጀምረው? ህጉ የሚለው የሚሾምን ሰው ሥራ አስኪያጁ ያቀርባል ፓትርያርኩ ይሾማል ነው። አሁን ግን የምትሾሙ የምትሽሩ እናንተ ሆናችኋል። ታዲያ እኔ የእናንተ አሻንጉሊት ነኝ? ስልጣኔ ምን እንደሆነ በዛሬው እለት እንድታሳውቁኝ እፈልጋለሁ። እስከዚያው ግን ስብሰባውን አልመራም» ብለው ከስብሰባው መውጣታቸውን ምንጮቻችን ተናግረዋል። አባ ሳሙኤል «እኛ ላይ እኮ በድረገጽ እየተጻፈብንና ስማችን እየጠፋ ነው» በማለት ሊያግባቧቸው ቢሞክሩም ብፁእነታቸው ፈቃደኛ አልሆኑም። የቋሚ ሲኖዶስን ስልጣን በጎን ቀምቶ ፈላጭ ቆራጭ እኔ ነኝ የሚለው የእነ «አባ» ሳሙኤል ቡድን አላንቀሳቅስ ካላቸውና ስልጣናቸው የሚፈቅድላቸውን ስራ እንዳይሰሩ ካደረጋቸው ወዲህ በአቃቤ መንበሩና በዚህ ቡድን መካከል ውጥረቱ እያየለ መጥቷል። የዛሬውም አቃቤ መንበሩ ከስብሰባው መውጣት ውጥረቱ የደረሰበትን ከፍተኛ ደረጃ የሚያሳይ ነው ይላሉ ታዛቢዎች።

ቡድኑን እያሽከረከሩ ያሉትና ለታላቅ አባት ያላቸውን ንቀት መስቀል ባለመሳለም የሚያሳዩት «አባ» ሳሙኤል በዛሬው እለት የአቃቤ መንበሩን መስቀል ሳይሳለሙ መቀመጣቸውን የተናገሩት ምንጮቻችን፥ ይህን የንቀትና የትእቢት ተግባር በብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ጳውሎስ ላይ ሲፈጽሙ እንደነበርና ቅዱስነታቸውን አቃጥለው ለሞት እንዳበቋቸው ሁሉ አቃቤ መንበሩም ላይ ተመሳሳይ ነገር እንዳይፈጸም ስጋታቸውን የሚገልጹ አሉ። እንዲያውም አቃቤ መንበሩ አንድ ነገር ቢሆኑ አባ ፊልጶስና ሶስቱ የጉድ ሙዳዮች - አባ ሳሙኤል አባ ሉቃስና አባ አብርሃም ተጠያቂዎች መሆን እንዳለባቸው ይጠቁሟሉ።

የቋሚ ሲኖዶስን ስልጣን የቀማውን ቡድን እንዲሰይሙ አቡነ ናትናኤልን ያግባባቸው የእርሳቸው ቀራቢ የነበረው የቀድሞው የማኅበረ ቅዱሳን ሰብሳቢ / ሙሉጌታ ስዩም ሲሆን፣ እንዲህ የተደረገውም «ሌሎች ቀድመውኝ ቢያወሩትም እኔጋ ግን ያለው በምስልና በድምጽ የተደገፈ መረጃ ነው» በሚል ማቅ የህሊና እስረኛ ያደረጋቸውንና በጥቅም የያዛቸውን ጳጳሳት እዚህ ቡድን ውስጥ እንዲካተቱ በማድረግ እንዳዋቀረው ለጉዳዩ ቅርበት ያላቸው ምንጮች ገልጸዋል። በአሁኑ ወቅት እያረቀቁ ያለው ህግም ፓትርያርኩ ከመባረክ ውጪ ምንም ስልጣን እንዳይኖረው የሚያደርግ እንደሆነና በዚህ በኩል ማቅ አስተዳደሩን ለመቆጣጠር እንዲያመቸው በወኪሎቹ በኩል እየሰራ መሆኑ ታውቋል። በአቃቤ መንበሩ ላይ የጳጳሳቱ ቡድን እያሳየ ያለውም በቀጣዩ ፓትርያርክ ላይ ሊያደርጉ ያቀዱትን ነው የሚሉ አሉ። በአሁኑ ሰአት አቃቤ መንበር ብፁዕ አቡነ ናትናኤል ከመባረክ ውጪ በስልጣናቸው ምንም እያደረጉ አይደለም።

ይህ በእንዲህ እንዳለ አቡነ ፊልጶስ የአቡነ ናትናኤልን መስቀል ሊሳለሙ ሲቀርቡ «ዞር በሉ» ብለው ፊት እንደነሷቸው ምንጮቻችን ገልጸዋል። እየማሉ በመካድ የሚታወቁት አባ ፊልጶስ ዘመዶቻቸውንና የወንዛቸውን ልጆች በአሁኑ ወቅት ቦታ ቦታ እያስያዙ መሆናቸውና ይህም ህግን ተከትሎ ማለትም እርሳቸው ለአቃቤ መንበሩ አቅርበው በአቃቤ መንበሩ መሾም ሲገባቸው አቃቤ መንበሩን ከጨዋታ ውጪ በማድረግ ውስጥ ውስጡን ሥራቸውን እየሰሩና ለይምሰል ግን መስቀላቸውን ለመሳም መቅረባቸው ስላናደዳቸው ነው አቃቤ መንበር ናትናኤል አባ ፊልጶስን ፊት የነሷቸው ተብሏል። አባ ፊልጶስ ሁለት እህቶቻቸውን በቅርቡ እያንዳንዳቸውን 3700 ብር ደሞዝተኛ አድርገው ወደላሊበላ መላካቸው ታውቋል። እያደረጉ ባለው ሹም ሽርም በአቡነ ጳውሎስ ጊዜ አስተዳደር ላይ ይሰሩ የነበሩትን ቀሲስ ዮሐንስን ከቦታቸው አንስተው ተንሳፋፊ ያደረጓቸው ሲሆን ጉባኤ አርድእትን ለማፍረስ በዋናነት የማቅ እጅ ሆኖ ያገለገለውን ሰለሞን ቶልቻን በቦታው ተክተዋል። 

በተያያዘም የማኅበረ ቅዱሳን ድረገጽ ደጀሰላም አንድ ጊዜ «የኦሮሞ ተወላጅ ፓትርያርክ ለማስቀመጥ እየሰሩ ነው፡፡» በሌላ ጊዜ ሌላ የስም ማጥፋት ዘመቻ ከፍቶባቸው የነበሩትን ቀሲስ በላይ መኮንንን ከጳውሎስ መንፈሳዊ ኮሌጅ ዲንነት እንዲነሱ ከአባ ፊልጶስ ደብዳቤ የተጻፈላቸው መሆኑ ታውቋል። ከደብዳቤው መጻፍ በፊት የቀረበው ምክንያትም ብሄራቸውን በሚነካ መልኩ «እርሱ የጳውሎስ ኮሌጅ ዲን ሊሆን አይገባም» የሚል መሆኑ ታውቋል። ቀሲስ በላይ ውሳኔውን እንደማይቀበሉ እየተናገሩ ነው ተብሏል። በዚህ ሁሉ ውስጥ ማኅበረ ቅዱሳንና የጳጳሳቱ ቡድን  ምን ያህል ተቀናጅተው እየሰሩ እንደሆነ እየታየ ነው።

ከታሪካቸው መበላሸት የተነሳ ፓትርያርክ የመሆን ህልማቸው እንደማይሳካ የተረዱት «አባ» ሳሙኤል በቀጣይ ልማት ኮምሽንን ለቀው የኢየሩሳሌም ጳጳስ መሆን እንደሚፈልጉ ምንጮቻችን ተናግረዋል።

No comments:

Post a Comment