Monday, March 19, 2012

ዘመድኩን ተጨማሪ ቅጣት ይጠብቀዋል


ደስታ ጌታሁን የ7 ወር እሥራት ተፈርዶበታል ግን. . .

አርማጌዶን በተባለ የተጭበረበረ ቪሲዲ አማካይነት በመጋቤ ሀዲስ በጋሻው ደሳለኝ ላይ የጥላቻና ስም ማጥፋት ዘመቻ ከፍቶ የነበረው ዘመድኩን በቀለ መጋቢት 6 ቀን 2004 ዓ.ም በዋለው የቦሌ ምድብ ችሎት የጥፋተኝነት ውሳኔ ተላለፈበት፡፡ ያለሥልጣኑ የቤተክርስቲያንን አገልጋዮች ሲዘልፍ የከረመው ዘመድኩን በአራዳ ምድብ ችሎት የ5 ወራት እሥራት የተቀጣ ሲሆን፣ በተመሳሳይ ሁኔታም በቦሌ ምድብ ችሎት ተጨማሪ ቅጣት እንደሚያገኘው ታውቋል፡፡

በዕለቱ የፍርድ ማቅለያ ሃሣብ እንዳለው የተጠየቀው ዘመድኩን "በጋሻው ቅን እና ጥሩ ሰው መሆኑን አውቃለሁ፡፡ እኛን ያጣላን የሃይማኖት ጉዳይ ነው. . . " ብሎ ሊዘረዝር ሲል፣ "ይህ እኮ የማጣራት ችሎት አይደለም፡፡ የፍርድ ማቅለያ ሃሣብ ካለህ እንድትገልጽ ነው ዕድሉ የተሰጠህ፡፡ ስለዚህ ወደ ሃሣቡ ግባ" ሲባል፣ "የልጆች አባት ነኝ፤ የቤተሰብ አስተዳዳሪ ነኝ" በማለት የተለመደ ሃሣቡን አቅርቧል፡፡ ዐቃቤ ሕግ በበኩሉ በሰጠው የቅጣት ማክበጃ ሃሣብ ዘመድኩን በሠራው ሥራ የማይጸጸትና ከስህተቱ ለመማር ዝግጁ ያልሆነ፣ ክሱ በሂደት እያለ እንኳን ሌላ የ"አርማጌዶን" ቪሲዲ ተከታይ ክፍል ማሳተሙ ለፍርዱ ሂደት ያለውን ንቀት ያሳያል፡፡

በፍርድ ቀጠሮ ቀናት በመቅረትና በማርፈድ ፍርድ ማጓተቱ ለፍርዱ ሂደት ያለውን አለመታዘዝ ያሳያል፡፡ ከዚህም በላይ ባሠራጨው የ"አርማጌዶን" ቪሲዲ ምክንያት ቤተክርስቲያን ለረጅም ጊዜ ውዝግብ ውስጥ መግባቷን እና በምዕመናን መካከል የክፍፍልና የጥርጥር መንፈስ መዝራቱን፣ ባጠቃላይ ወደ አምስት የሚሆኑ ማክበጃ ነጥቦችን የዘረዘረ ሲሆን፣ ግንቦት 13 ቀን 2004 .ም ተወሰነው ቀጣይ ቀጠሮም የቅጣት ውሳኔ እንደሚጣልበት ይጠበቃል፡፡

በሌላ በኩል "የሰባኪው ህጸጽ" በሚል ርዕስ መጽሐፍ አሳትሞ መጋቤ ሀዲስ በጋሻው ደሳለኝን በግል የበደለው ደስታ ጌታሁን የ7 ወራት እሥራት የተፈረደበት ሲሆን፣ በመታሠሩ ምክንያት ከሥራ እንደሚፈናቀል፣ የቤተሰብ አስተዳዳሪ እና ባለቤቱ ከወለደች 3 ቀናት ብቻ የሆናት መሆኑን አልቅሶ ለፍርድ ቤት ገልጾ፣ ችግሩን ከቀበሌ በተጻፈ ማስረጃ አስደግፏል፡፡ በቅጣት ውሳኔውም ዕለት ሆድ በሚያባባ ተማጽኖ ፍርድ ቤቱን ያስጨነቀው ደስታ የ7 ወራት እሥር ቅጣቱ ወደ 2 ዓመት ገደብና የ3 ሺህ ብር ቅጣት እንዲሁም ለ2 ዓመቱ ገደብ 5ሺህ ብር ዋስትና ተለውጦለት ሊወጣ ችሏል፡፡ ደስታ ከዚህ በኋላ ምላሱን መሰብሰብ ያለበት ሲሆን በተመሳሳይ ወንጀል ውስጥ ራሱን ቢዘፍቅ ያስያዘው ብር ከመቅለጡም በላይ የተፈረደበት የ7 ወራት ቅጣት በዕጥፍ ሆኖ ይጠብቀዋል፡፡

No comments:

Post a Comment