Thursday, November 22, 2012

ወደ ፍ/ቤት ሽማግሌ ይላካል አይላክም በሚል «አባ» ሳሙኤልና ጠበቆቻቸው ሳይስማሙ ቀሩ


ምንጭ:- አባ ሰላማ ብሎግ
Wednesday, November 21, 2012


የአባ ሚካኤል አስከሬን ወጥቶ እንዲመረመር ፍርድ ቤት ከወሰነ ወዲህ ከፍተኛ ድንጋጤ ውስጥ የገቡትና ነገሩን በሽማግሌ ለመጨረስ እየተንቀሳቀሱ ያሉት «አባ» ሳሙኤል ወደ /ቤት ይሄዱልኛል ያሏቸውን ሽማግሌዎች ያዘጋጁ ቢሆንም በጠበቆቻቸው በኩል ግን ሀሳቡ ተቀባይነት ሳያገኝና ሽማግሌም ሳይላክ መቅረቱ ተነግሯል፡፡ በጠበቆቹ በኩል የቀረበው ሐሳብ ተገቢነት ያለውና ህጋዊውን መንገድ የተከተለ  ሲሆን፣ «አባ» ሳሙኤልን «እርስዎ ጳጳስ ሆነው የሽምግልና ሕግን እንዴት አያውቁም? ሽምግልና እኮ እየተካሰሱ ባሉት ሁለት ወገኖች መካከል የሚከናወን የእርቅ ሂደት እንጂ ከፍርድ ቤት ጋር አይደለም፡፡ በፍ/ቤት ሕግ እንዲህ አይነት ሽምግልና ተሰምቶም ታይቶም አያውቅም» ብለዋቸዋል ተብሏል፡፡ አክለውም «ሽማግሌ መላክ ካለብንም መላክ የምንችለው የአባ ሚካኤል ልጅ ነኝ ወደሚለው ወደ ዮሐንስ ነው፡፡» ብለዋል፡፡

ይህን መቀበልና ከዮሐንስ ጋር ያላቸውን የክስ ሂደት በሽማግሌ መጨረስ ሽንፈትና ሞት መሆኑን የተረዱት «አባ» ሳሙኤል ግን ሐሳቡን መቀበል አልፈለጉም፡፡ ምክንያቱም ነገሩን በሽማግሌ መጨረስ የሚቻለው ዮሐንስ የአባ ሚካኤል ልጅ መሆኑን በመቀበል መሆኑ ሳይታለም የተፈታ ነው፡፡ ለነገሩ በተደጋጋሚ ለመግለጽ እንደሞከርነው አባ ሚካኤል ልጃቸው መሆኑን ሳይክዱ እየረዱ እንዳሳደጉትና ለቁም ነገር እንዳበቁት «አባ» ሳሙኤልም ጭምር የታወቀ ነው፡፡ ይህ ነገር ይፋ መውጣቱ ግን ምእመናን ለጳጳሳት ያላቸው ክብር ግምት እንዲቀንስ የሚያደርግ በመሆኑ ከዮሐንስ ጋር ነገሩን በሽምግልና መጨረስ የማይታሰብ ነገር ነው፡፡ ውሳኔውን መቀበልም በሕግ ፊት የነገሩን እውነተኛነት ማረጋገጥ ነው፡፡ ከሁለቱ ክፉ ምርጫዎች የቱን እንደሚመርጡ የተቸገሩ የሚመስሉት «አባ» ሳሙኤል ሽማግሌ መላክ አለበት በሚለው አቋማቸው እንደጸኑ መሆናቸውን ለጉዳዩ ቅርበት ያላቸው ሰዎች እየተናገሩ ነው፡፡ ሳይማሩ የጠመጠሙት «አባ» ሳሙኤል ሽማግሌዎቹን እኔ አዘጋጅቻለሁ እናንተ የፍ/ቤቱን መንገድ ስለምታውቁት መንገዱን አሳዩኝ ብለው በአቋማቸው ቢጸኑም ጠበቆቹ የአባ ሳሙኤል ሀሳብ ከአንድ ጳጳስ የማይጠበቅና ያልተማረ ሰው እንኳን ያስበዋል ተብሎ የማይጠበቅ በመሆኑና /ቤትም በህግ የያዘውን ጉዳይ በህግ አግባብ ከመጨረስ በቀር የተጣላውና የተካሰሰው ወገን ስለማይኖር ሽምግልና የሚባል ነገር ስለማያስተናግድና ሀሳቡ ህጋዊ ባለመሆኑ ውድቅ በማድረግ ሳይተባበሯቸው ቀርተዋል፡፡


በዚህ የተበሳጩት «አባ» ሳሙኤል «እኔ እያመመኝ ነው፤ ዕረፍት ማድረግ አለብኝ» በሚል ወደ ኢየሩሳሌም መሄዳቸው ተሰምቷል፡፡ ምናልባትም በዚህ ሰበብ የፍርዱን የመጨረሻ ውሳኔ ላለማየት በሚል ይሁን ወይም በእርግጥ አሟቸው ለጊዜው የታወቀ ነገር ግን የለም፡፡

Friday, November 16, 2012

ሰበር ዜና: የአባ ሚካኤል አስከሬን ተቆፍሮ እንዳይወጣ ለማድረግ «አባ» ሳሙኤል ወደ ፍርድ ቤት ሽማግሌ ሊልኩ መሆናቸው ተሰማ


ምንጭ:- አባ ሰላማ ብሎግ
Thursday, November 15, 2012

ሰኞ ዕለት ባወጣነው ዘገባ እንደ ገለጽነው የልደታ ምድብ ችሎት ባለፈው አርብ የአባ ሚካኤል አስከሬን ወጥቶ የዲኤንኤ ምርመራ እንዲካሄድበት ወስኗል፡፡ ይህን ውሳኔ ተከትሎ እውነት የምትገለጥበት ጊዜ መቅረቡ ያሳሰባቸውና የሚይዙ የሚጨብጡትን አጥተው የሰነበቱት «አባ» ሳሙኤል በዓለም ታሪክ ታይቶም ተሰምቶም በማያውቅ አሰፋሪ ሁኔታ ሲኖዶስ ወስኖ በደብዳቤ የጠየቀውንና ከፍርድ ቤት በኩል ምላሽ ያጣበትን ጉዳይ በሽምግልና ለመጨረስ በማሰብ ዛሬ ኅዳር 6/2005 . ለፍርድ ቤት ሽማግሌ ለመላክ መወሰናቸውንና ለዚሁ ጉዳይ እየተንቀሳቀሱ መሆናቸውን ለጉዳዩ ቅርበት ያላቸው ምንጮች ገለጹ፡፡


እንደ ምንጮቻችን ከሆነ «አባ» ሳሙኤል ሽማግሌ ለመላክ እየተንቀሳቀሱ ያሉት ከማንያዘዋል ጋር በመሆን በፍርድ ቤት አካባቢ የሚገኙና ከማኅበረ ቅዱሳን ጋር ንክኪ ያላቸውንና የማኅበሩ አባላት የሆኑ ዳኞችንና የህግ ሰዎችን በማሳመን የአባ ሚካኤል አስከሬን ተቆፍሮ እንዳይወጣ እንዲያደርግና ፍርድ ቤቱም ከአሁን በኋላ ጉዳዩ የሃይማኖት ነውና አይመለከተኝም ብሎ ፋይሉን እንዲዘጋ ለማድረግ ነው፡፡ ዋና የማሳመኛ ነጥብ አድርገው ያቀርባሉ ተብሎ የሚጠበቀው «የአባ ሚካኤል አስከሬን ወጥቶ እንዲመረመር ከተደረገ ቤተክርስቲያን ትዋረዳለች፤ ስለዚህ ቤተክርስቲያን እንዳትዋረድ ይህ ጉዳይ እንዳይነሣ ተደርጎ መቀበር አለበት» የሚል ነው፡፡ ይሁን እንጂ ይህን እውነት በማፈን ቤተክርስቲያን ትዋረዳለች እንጂ አትከበርም፡፡ እንዲህ ያለውን የቆብ ውስጥ ገበና በመግለጥ በእግዚአብሔር ቃል ውስጧን ብተፈትሽና ችግሮቿን ብትፈታ ወደእግዚአብሔርም ፊቷን ብትመልስ ነው ለቤተክርስቲያን ክብሯ፡፡ ጉዳዩ የሚዲያ ሽፋን ያገኘና ቤተክርስቲያን ውስጥ በይፋ የሚታወቅ ጉዳይ በመሆኑ፣ አባ ሚካኤል ያልካዱትንና ተቀብለው ልጃቸውን በማሳደግ ለቁም ነገር ያበቁበትን ይህን እውነት ለማፈን የሚደረገው ሩጫ ለቤተክርስቲያን ከማሰብ ሳይሆን በአባ ሚካኤል የተጀመረው ይህ ጉዳይ፣ ወደሌሎቹ ተረኞች እንዳይዛመት በተለይም የእነ«አባ» ሳሙኤልን ጸሐይ የሞቀውና አገር ያወቀው እንኳን ከጵጵስና ከደህና አቶነት ውጪ የሚያደርገው የተበላሸ ታሪክ ከአሁኑ የበለጠ ጉዳት እንዳይደርስበት በማሰብ እንደሆነ ብዙዎች ይስማማሉ፡፡

«አባ» ሳሙኤል በታሪክ ተሰምቶም ተደርጎም የማያውቀውን በሕግ ብቻ የሚሠራውን ፍርድ ቤትን በሽምግልና ለመጠምዘዝ የጀመሩት ጉዞ ሰውዬው የሚገኙበትን ደረጃ ፍንትው አድርጎ የሚያሳይ ነው፡፡ ጉዳዩ በሽምግልና እንዲያልቅ ከተፈለገም መደረግ የነበረበት ከአባ ሚካኤል ህጋዊ ልጅ ከዮሐንስ ሚካኤል ጋር መደራደርና ስምምነት መፍጠር ከዚያም በሁለቱ ወገኖች ስምምነት ጉዳዩን ፍርድ ቤቱ እንዳቋርጥ ማድረግ ነበር፡፡ ማንአለብኙ «አባ» ሳሙኤል ግን ይህን ህጋዊ መንገድ ትተው በሕግ ብቻ የሚመራውንና በህግ መሰረት ብይን የሚሰጠውን ፍርድ ቤትን እንሸማገል ብለው ለመጠየቅ መነሳታቸው ብዙዎችን አስገርሟል፡፡ ፍትህን በአመጽ መንገድ እንጂ በትክክለኛውና በእውነተኛው መንገድ ማግኘት የማይችሉና የማይፈልጉም መሆናቸውንም አስመስክሯል፡፡

ጉዳዩ በእውነተኛ ፍርድ እስካልተቋጨ ድረስ የማያርፉትና ከጳጳስ በማይጠበቅ ሁኔታ ምእመናንን በአለም ፍርድ ቤት በመክሰስና በመካሰስ ወደር ያልተገኘላቸው «አባ» ሳሙኤል በገንዘብ ሃይል ጭምር ይህን አጣብቂኝ ውስጥ የገባ ጉዳይ አፍኖ ህገወጥ መንገዶችን ሁሉ በመጠቀም ለማስቀረት የማቆፍሩት ጉድጓድ እንደማይኖር ምንጮቻችን ተናግረዋል፡፡ በዚህ ረገድ ልምድ ካለው ማኅበረ ቅዱሳን ጋር ግንባር መፍጠራቸው ደግሞ አንዳንዶችን አሳስቧል፡፡ ለዚህም የፍርድ ሂደቶችን በህገወጥ መንገዶች እንዲቋረጡ በማድረግ የተካነው ማህበረ ቅዱሳን የህግ ሰው ሆኖ ሳለ የቀድሞው አባሉ «ዲያቆን» የአሁኑ «ቄስ» (ዲቁናውም ቅስናውም የክብር ነው) እሸቱ ታደሰ ናዝሬት ላይ የፈጸመውን ሴቶችን የመድፈር፣ ገንዘብ የማጭበርበርና የነፍስ ግድያ ሙከራ ወንጀል በፖሊስ ፕሮግራም ሲተላለፍ ቆይቶ የት እንደደረሰ ሳይታወቅ ጉዳዩ ተድበስብሶ እንዲቀር እንዳደረገና እሸቱ ተገቢውን ቅጣት ሳያገኝ 8 ወራት እስራት በኋላ በዋስ ተፈቶ ወዲያው የሐመር መጽሔት አዘጋጅ ሆኖ መሾሙን ያስታውሳሉ፡፡ ይሁን እንጂ የአባ ሚካኤልን ጉዳይ የያዘው ፍርድ ቤቱ ውሳኔውን ለውጦ «አባ» ሳሙኤልን ምድር ላይ የሌለ «ሽምግልና» ተቀብሎ የፍርድ ሂደቱን ያቋርጣል የሚል ሐሳብ እንደሌላቸው ብዙዎች ግምታቸውን ይናገራሉ፡፡ ለሁሉም ጉዳዩ የደረሰበትን እየተከታተልን ለመዘገብ እንሞክራለን፡፡

እርማት    
ሰኞ እለት ባወጣነው የአባ ሚካኤል ዘገባ ላይ የፍርድ ሂደቱ የተካሄደው ሐሙስ እለት ነው የሚለው በስሕተት ስለሆነ አርብ በሚለው እንዲስተካከል፣ ሶስተኛ አንቀጽ ላይም ««አባ» ሳሙኤል መሪነት ሲከራከሩ የነበሩት የአባ ሳሙኤል የስጋ ዘመዶች» የሚለው «የአባ ሚካኤል የሥጋ ዘመዶች» በሚለው እንዲስተካከል በታላቅ ትህትና ይቅርታ እንጠይቃለን፡፡