Friday, November 16, 2012

ሰበር ዜና: የአባ ሚካኤል አስከሬን ተቆፍሮ እንዳይወጣ ለማድረግ «አባ» ሳሙኤል ወደ ፍርድ ቤት ሽማግሌ ሊልኩ መሆናቸው ተሰማ


ምንጭ:- አባ ሰላማ ብሎግ
Thursday, November 15, 2012

ሰኞ ዕለት ባወጣነው ዘገባ እንደ ገለጽነው የልደታ ምድብ ችሎት ባለፈው አርብ የአባ ሚካኤል አስከሬን ወጥቶ የዲኤንኤ ምርመራ እንዲካሄድበት ወስኗል፡፡ ይህን ውሳኔ ተከትሎ እውነት የምትገለጥበት ጊዜ መቅረቡ ያሳሰባቸውና የሚይዙ የሚጨብጡትን አጥተው የሰነበቱት «አባ» ሳሙኤል በዓለም ታሪክ ታይቶም ተሰምቶም በማያውቅ አሰፋሪ ሁኔታ ሲኖዶስ ወስኖ በደብዳቤ የጠየቀውንና ከፍርድ ቤት በኩል ምላሽ ያጣበትን ጉዳይ በሽምግልና ለመጨረስ በማሰብ ዛሬ ኅዳር 6/2005 . ለፍርድ ቤት ሽማግሌ ለመላክ መወሰናቸውንና ለዚሁ ጉዳይ እየተንቀሳቀሱ መሆናቸውን ለጉዳዩ ቅርበት ያላቸው ምንጮች ገለጹ፡፡


እንደ ምንጮቻችን ከሆነ «አባ» ሳሙኤል ሽማግሌ ለመላክ እየተንቀሳቀሱ ያሉት ከማንያዘዋል ጋር በመሆን በፍርድ ቤት አካባቢ የሚገኙና ከማኅበረ ቅዱሳን ጋር ንክኪ ያላቸውንና የማኅበሩ አባላት የሆኑ ዳኞችንና የህግ ሰዎችን በማሳመን የአባ ሚካኤል አስከሬን ተቆፍሮ እንዳይወጣ እንዲያደርግና ፍርድ ቤቱም ከአሁን በኋላ ጉዳዩ የሃይማኖት ነውና አይመለከተኝም ብሎ ፋይሉን እንዲዘጋ ለማድረግ ነው፡፡ ዋና የማሳመኛ ነጥብ አድርገው ያቀርባሉ ተብሎ የሚጠበቀው «የአባ ሚካኤል አስከሬን ወጥቶ እንዲመረመር ከተደረገ ቤተክርስቲያን ትዋረዳለች፤ ስለዚህ ቤተክርስቲያን እንዳትዋረድ ይህ ጉዳይ እንዳይነሣ ተደርጎ መቀበር አለበት» የሚል ነው፡፡ ይሁን እንጂ ይህን እውነት በማፈን ቤተክርስቲያን ትዋረዳለች እንጂ አትከበርም፡፡ እንዲህ ያለውን የቆብ ውስጥ ገበና በመግለጥ በእግዚአብሔር ቃል ውስጧን ብተፈትሽና ችግሮቿን ብትፈታ ወደእግዚአብሔርም ፊቷን ብትመልስ ነው ለቤተክርስቲያን ክብሯ፡፡ ጉዳዩ የሚዲያ ሽፋን ያገኘና ቤተክርስቲያን ውስጥ በይፋ የሚታወቅ ጉዳይ በመሆኑ፣ አባ ሚካኤል ያልካዱትንና ተቀብለው ልጃቸውን በማሳደግ ለቁም ነገር ያበቁበትን ይህን እውነት ለማፈን የሚደረገው ሩጫ ለቤተክርስቲያን ከማሰብ ሳይሆን በአባ ሚካኤል የተጀመረው ይህ ጉዳይ፣ ወደሌሎቹ ተረኞች እንዳይዛመት በተለይም የእነ«አባ» ሳሙኤልን ጸሐይ የሞቀውና አገር ያወቀው እንኳን ከጵጵስና ከደህና አቶነት ውጪ የሚያደርገው የተበላሸ ታሪክ ከአሁኑ የበለጠ ጉዳት እንዳይደርስበት በማሰብ እንደሆነ ብዙዎች ይስማማሉ፡፡

«አባ» ሳሙኤል በታሪክ ተሰምቶም ተደርጎም የማያውቀውን በሕግ ብቻ የሚሠራውን ፍርድ ቤትን በሽምግልና ለመጠምዘዝ የጀመሩት ጉዞ ሰውዬው የሚገኙበትን ደረጃ ፍንትው አድርጎ የሚያሳይ ነው፡፡ ጉዳዩ በሽምግልና እንዲያልቅ ከተፈለገም መደረግ የነበረበት ከአባ ሚካኤል ህጋዊ ልጅ ከዮሐንስ ሚካኤል ጋር መደራደርና ስምምነት መፍጠር ከዚያም በሁለቱ ወገኖች ስምምነት ጉዳዩን ፍርድ ቤቱ እንዳቋርጥ ማድረግ ነበር፡፡ ማንአለብኙ «አባ» ሳሙኤል ግን ይህን ህጋዊ መንገድ ትተው በሕግ ብቻ የሚመራውንና በህግ መሰረት ብይን የሚሰጠውን ፍርድ ቤትን እንሸማገል ብለው ለመጠየቅ መነሳታቸው ብዙዎችን አስገርሟል፡፡ ፍትህን በአመጽ መንገድ እንጂ በትክክለኛውና በእውነተኛው መንገድ ማግኘት የማይችሉና የማይፈልጉም መሆናቸውንም አስመስክሯል፡፡

ጉዳዩ በእውነተኛ ፍርድ እስካልተቋጨ ድረስ የማያርፉትና ከጳጳስ በማይጠበቅ ሁኔታ ምእመናንን በአለም ፍርድ ቤት በመክሰስና በመካሰስ ወደር ያልተገኘላቸው «አባ» ሳሙኤል በገንዘብ ሃይል ጭምር ይህን አጣብቂኝ ውስጥ የገባ ጉዳይ አፍኖ ህገወጥ መንገዶችን ሁሉ በመጠቀም ለማስቀረት የማቆፍሩት ጉድጓድ እንደማይኖር ምንጮቻችን ተናግረዋል፡፡ በዚህ ረገድ ልምድ ካለው ማኅበረ ቅዱሳን ጋር ግንባር መፍጠራቸው ደግሞ አንዳንዶችን አሳስቧል፡፡ ለዚህም የፍርድ ሂደቶችን በህገወጥ መንገዶች እንዲቋረጡ በማድረግ የተካነው ማህበረ ቅዱሳን የህግ ሰው ሆኖ ሳለ የቀድሞው አባሉ «ዲያቆን» የአሁኑ «ቄስ» (ዲቁናውም ቅስናውም የክብር ነው) እሸቱ ታደሰ ናዝሬት ላይ የፈጸመውን ሴቶችን የመድፈር፣ ገንዘብ የማጭበርበርና የነፍስ ግድያ ሙከራ ወንጀል በፖሊስ ፕሮግራም ሲተላለፍ ቆይቶ የት እንደደረሰ ሳይታወቅ ጉዳዩ ተድበስብሶ እንዲቀር እንዳደረገና እሸቱ ተገቢውን ቅጣት ሳያገኝ 8 ወራት እስራት በኋላ በዋስ ተፈቶ ወዲያው የሐመር መጽሔት አዘጋጅ ሆኖ መሾሙን ያስታውሳሉ፡፡ ይሁን እንጂ የአባ ሚካኤልን ጉዳይ የያዘው ፍርድ ቤቱ ውሳኔውን ለውጦ «አባ» ሳሙኤልን ምድር ላይ የሌለ «ሽምግልና» ተቀብሎ የፍርድ ሂደቱን ያቋርጣል የሚል ሐሳብ እንደሌላቸው ብዙዎች ግምታቸውን ይናገራሉ፡፡ ለሁሉም ጉዳዩ የደረሰበትን እየተከታተልን ለመዘገብ እንሞክራለን፡፡

እርማት    
ሰኞ እለት ባወጣነው የአባ ሚካኤል ዘገባ ላይ የፍርድ ሂደቱ የተካሄደው ሐሙስ እለት ነው የሚለው በስሕተት ስለሆነ አርብ በሚለው እንዲስተካከል፣ ሶስተኛ አንቀጽ ላይም ««አባ» ሳሙኤል መሪነት ሲከራከሩ የነበሩት የአባ ሳሙኤል የስጋ ዘመዶች» የሚለው «የአባ ሚካኤል የሥጋ ዘመዶች» በሚለው እንዲስተካከል በታላቅ ትህትና ይቅርታ እንጠይቃለን፡፡



No comments:

Post a Comment