Thursday, March 8, 2012

የ"ማኅበረ ቅዱሳን" ስልታዊ ፀረ መንግሥት ውጊያ


ማኅበረ ቅዱሳን ከሰሞኑ «አንድ አድርገን» በተባለው ብሎጉ የዋልድባ ገዳምን በተመለከተ ሐተታ ያቀረበ ሲሆን፣ ከማኅበሩ አካባቢ የተቀሰቀሰው የአቧራ ብናኝ በየሥፍራው ብቅ ብቅ ማለቱን ስናይ እስቲ ተረጋጋና ቁጭ ብለን እንወያይበት ልንለው ወደድን፡፡

ማኅበረ ቅዱሳን ሰኞ የካቲት 26 ቀን ‹‹እናንተ ደፋሮች ይህን ጉዳይ ብላችሁ የአንድን ሀገር መሪ ልታናግሩ መጣችሁ ›› ለዋልድባ ገዳም መነኮሳት 4ኪሎ ቤተመንግስት የተሰጠ ምላሽ» በሚል ርዕስ ባቀረበው ሐተታ መንግሥት ሆን ብሎ ቤተክርስቲያናችንንና ገዳማችንን ለማጥፋት ዘመቻ ከፍቷል የሚል ነው፡፡ ከዚህም ጋር ተያይዞ ወደ ቤተመንግሥት ተጉዘው ለጠቅላይ ሚኒስትሩ ማመልከቻቸውን ለማቅረብ የሄዱ አባቶች ካሀናትና መነኮሳት ‹‹እናንተ ደፋሮች ይህን ጉዳይ ብላችሁ የአንድን ሀገር መሪ ልታናግሩ መጣችሁ ›› ተብለው ተናቁብን፤ እኛም ተናቅን፡፡ ሰለዚህ በዓለም ላይ የምንገኝ የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተክርስቲያን ተከታዮች ተነሱ፤ ታገሉ የሚል ቅስቀሳ አድርጓል፡፡

እንደ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተክርስቲያን አማኝነታችን እኛም የዋልድባ ገዳም እንዲከበር እንፈልጋለን፡፡ መንግሥትም ይህንን እንደሚረዳ እናምናለን፡፡ ምክንያቱም በሕገ መንግሥቱ እንደተደነገገው የእምነትና የአምልኮ ሥፍራዎች ጥበቃ ይደረግላቸዋል፡፡ ክብርም ይሰጣቸዋል፡፡ ይሄ መብት ለሁሉም ሃይማኖቶችና ቤተእምነቶች በእኩልነት እንዲያገለግል የተደነገገ ነው፡፡
ይሁን እንጂ፣ ዋልድባ ገዳምን በተመለከተ የስኳር ፋብሪካ ሲጠና በባህል፣ በሕብረተሰቡ፣ በአካባቢው ተፈጥሯዊ ይዘትና የአየር ንብረት ላይ የሚያደርሰው ተፅዕኖ ሳይጠና አይካሄድም፤ በዚህም እናምናለን፡፡ ሀኖም መንግሥት በተቃራኒው መንገድ ሄዶ በደመነፍስ ሊያፈርሰው ነው ብንል እንኳን ተነስ፣ ታጠቅ፣ ዝመት፣ በሚል ቅስቀሳ መፍትሔ ሊገኝ ይችላል ወይ? በፍጹም አይገኝም፡፡ 

የገዳም ኑሮ በዋሻና በዱር በገደል ስለሆነ መንግሥት ይህንን አፍርሶ፣ በዙሪያው ያለውን የተፈጥሮ ደን አራቁቶ ለኢንቨስትመንት የሚጠቅም ሰፊ መሬት ያገኛል፤ ሕዝብም በዚህ ይጠቀማል ብለን አናምንም፡፡ 

የተፈጠረው ችግር ዕልባት እንዲያገኝ ከተፈለገ፣ የሚያዋጣው ራስ ይዞ መጨኽና ዘራፍ ለሀገሬ፣ ዘራፍ ለማኅተሜ ከእምነቴ ጋር ድህነት ይሻለኛል ትራንስፎርሜሽን ገደል ይግባ የምንል ከሆነ የምናደርገውን አናውቅም ወይም በግርግር የዋሃን አማንያንን በቀውስ ውስጥ ዘፍቀን መንግሥትንና ፓትርያርኩን ገልብጠን አፍቃሬ ማኅበረ ቅዱሳን (ማኅበረ ቅዱሳናዊ) መንግሥትና ሲኖዶስ የማቋቋም ህልም አለን ማለት ነው፡፡

ሕግና ሥርዓትን የምናውቅ ከሆነ የቤተክርስቲያንንና የቅዱስ ሲኖዶስን ሕልውና፣ መዋቅርና አደረጃጀቱን አምነን መቀበል አለብን፡፡ የዋልድባ ገዳም የበላይ ጠባቂና የሀገረ ስብከቱ ሊቃነጳጳሳት እንዲሁም፣ ጠቅላይ ቤተክህነት ጽ/ቤት፣ ቅዱስ ሲኖዶስ ጽ/ቤትና መንበረ ፓትርያርክ ልዩ ጽ/ቤት በጉዳዩ ላይ መክረው ከመንግሥት ጋር መወያየት አያቅታቸውም፡፡ የሚፈታውም እንደዚያ ሲሆን ነው፡፡ 

ከዚህ አንፃር የገዳሙ ካሀናትና መነኮሳት ማኅበረ ቅዱሳን አገልግል አስይዞ አደራጅቶና ቀስቅሶ እንዳመጣቸው በቀጥታ ጠቅላይ ሚኒስትሩ ድረስ መሄድ አልነበረባቸውም፡፡ ጥያቄያቸውን በግልጽ፣ በመረጃ አስደግፈው ከታች ከወረዳ አስተዳደር ጀምረው ማቅረብ ሲገባቸው ክልል አስተዳደርንም፣ ጠቅላይ ቤተክህነትንም ዘለው ጠቅላይ ሚኒስትሩን እናነጋግራለን ቢሉ የጠቅላይ ሚኒስትሩ ሥራ ያ ብቻ አይደለምና ደፋሮች ባይባሉ እንኳን፣ ጠቅላይ ሚኒስትሩ አላነጋገሩንም ተብሎ በማኅበረ ቅዱሳን ብሎጎች ሊብጠለጠሉ አይገባም፡፡ 

በዋልድባ ገዳም አሳብቦ ፓትርያርኩንና መንግሥትን ማውገዝ፣ ጅብን ሊወጉ በአህያ ይጠጉ የሚለውን የአበው ብሂል ያስታውሰናል፡፡ የሆነው ሆኖ ማኅበረ ቅዱሳን ይህንን ሁሉ ጫጫታ ያበዛው ስለኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተክርስቲያን ሃይማኖታችን ተቆርቁሮ ሳይሆን የያዘው የሥልጣን ጥማትና የነፍጠኛነት የዞረ ድምር (Hangover) ነው፡፡ ዛሬ ዋነኛ የቤተክርስቲያናችን ቁልፍ ችግር፣ ለመፍረስም ፈተና የሆነባት የማኅበረ ቅዱሳን አልታዘዝ ባይነት፣ በአስተዳደራዊ መዋቅር ውስጥ ጣልቃ ገብቶ አላሠራ ማለቱና ስውር አደረጃጀቱ ነው፡፡

No comments:

Post a Comment